የጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የ90 ቀናት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ተካሄደ፡፡
የክፍለ ከተማውና የ10ሩም ወረዳዎች አመራሮች በተሳተፉበት በዚህ ግምገማ በዕቅዱ ልዩ ልዩ ዘርፎች የተከናወኑ ሥራዎች የ90 ቀናት ዕቅድ አፈጻጸምና የተገኙ ውጤቶች ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ግምገማውን የመሩት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ጀማሉ ጀምበር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ90 ቀናት ዕቅዱ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወንን የመገባደጃና ስራዎቻችን በተግባር የምናረጋግጥበት በመሆኑ ከጊዜ አንፃር ተግባራትን አቀናጅቶ የመምራትና በሁሉም ዘርፎች የተያዘውን ዕቅድ የማሳካት ቀዳሚ ኃላፊነት የአመራሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ ውጤቶች አበረታች መሆናቸውን ያመለከቱት ኃላፊው በተግባራቱ አፈጻጸም የሚታዩ ውስንነቶችና የወጥነት ችግር በፍጥነት ሊፈቱ እንደሚገባና ወረዳዎች እና ሴክተሮች ለተግባሩ ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አክለው አስገንዝበዋል፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወልዴ ወገሴ በበኩላቸው የ90 ቀናት ዕቅድን በክፍለ ከተማው ተፈጻሚ ለማድረግ ከፍ ያለ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸው፣ ዕቅዱን ለማስፈጸም የተዋቀሩ አካላትና የሚመለከታቸው ሴክተሮች የጀመሩትን እንቅስቃሴ በተቀናጀና በተናበበ አግባብ ማስቀጠል እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡
በሁሉም ተግባራት የሚመዘገበው ውጤት በቀጣይ ለሚከናወኑ ሥራዎች መሠረት መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸው፣ አመራሩ የመሪነት ሚናውን በላቀ ትጋት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ይከበር ስማቸው በበኩላቸው ዕቅዱን በማገባደድ ላይ የምንገኝ በመሆኑ አስፈጻሚ ግብረ ኃይሎች ሥራዎችን በአግባቡ ለይቶና ለፈጻሚ አካላት በማውረድ በሁሉም ደረጃ ወጥነት ያለው አፈጻጸም ለማስመዝገብ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አመራሩ ቅንጅታዊ አሠራርን ማጠናከር እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል፡፡