በጉለሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የ2018 ዓ.ም የገና ባዛርና ኤግዚቢሽን ተከፈተ።
በጉለሌ ክፍለ ከተማ " በቂ የምርት አቅርቦት በተመጣጣኝ ዋጋ ለሁሉም ሸማቾች ለገናችን !! " በሚል መሪ ሃሳብ የ2018 የገና በዓል ባዛርና ኤግዚቢሽን ተከፍቷል።
ባዛርና ኤግዚቢሽኑ በክፍለ ከተማው ፣ በንግድ ጽ/ቤት ፣በኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት፣ በአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ጽ/ቤት እንዲሁም በህብረት ስራ ጽ/ቤት በትብብር የተዘጋጀ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን በመክፈቻ ስነ- ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የባዛርና ኤግዚቢሽኑ መከፈት በአምራቹና በሸማቹ መካከል መተማመንን የሚፈጥር መሆኑን ጠቅሰው ምርትን በአደባባይ ማውጣት ደንበኛ ለማፍራትና የገበያ ትስስር ለመፍጠር እድል ይኖረዋል ብለዋል።
ከዚህ አኳያም ከተማ አስተዳደሩ መጪው የገና በዓል በሁሉም ክፍለ ከተሞች ባዛር በማዘጋጀት ማህበረሰቡ በዝቅተኛ ዋጋ ትኩስና ጥራቱን የተጠበቀ ምርት እንዲያገኝ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወልዴ ወገሴ በክፍለ ከተማው ያለውን የንግድ ስርዓት በማዘመን ነጋዴውንና ሸማቹን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል።
የኑሮ ውድነትን ለማቃለልና የምርት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት በእሁድ ገበያ ማዕከል ላይ ምርት በብዛትና በጥራት እንዲቀርብ ከማድረግ ባሻገር በሰንበት ገበያ መዳረሻ ቦታዎች ላይም የግብይት ስርዓቱን በማስፋት ለሸማቹ አስፈላጊ የሆኑ ምርቶች በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ እየተቻለ ነው ብለዋል።
መጪው የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ያልተገባ የዋጋ ጭማሬ እንዳይደረግ የክፍለ ከተማውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚያደርግ ባዛርና ኤግዚቢሽን የተከፈተ መሆኑን ተናግረዋል።
የክፍለ ከተማው ንግድ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ነጋሽ የኑሮ ውድነትን ለማቃለልና የምርት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት የሚያስችሉ ስራዎችን በማከናወን የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር አምራችና ሸማቹ በቀጥታ ግብይት የሚፈፅሙባቸው የሰንበት ገበያ መዳራሻ ስፍራዎች በማስፋት ረገድ ውጤታማ ስራ የተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ባዛርና ኤግዚቢሽኑ አምራቾች በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቶቻቸውን ለገበያ በማቅረብ እና በማስተዋወቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ባዛርና ኤግዚቢሽን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን የሚያነቃቃ እና የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።